ጽላሎት - yabeto

ጽላሎት

Regular price
$1.48
Sale price
$1.48
Regular price
Sold out
Unit price
per 
Shipping calculated at checkout.

Product Details

Synopses & Reviews

ቅኑና ደጉ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ብዙ መጻሕፍትን አበርክቶልናል፡፡አመሰግናለሁ፡፡ በተለይ "ማዕቀብ" እና "የበዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ" የሚለውን ጥናታዊ ሥራዎቹን እወዳቸዋለሁ፡፡ እንዳለጌታ በአጫጭር ጽሑፎቹ ልዩ ችሎታው በተለይ የሰዎችን ቁስልና ሕመም ራሱ ተጎጅ ላይ ቁሞ ሲጽፍ በጣም የሚገርም ነው፡፡ እንዳለጌታ የሰዎች ሕመም ሕመሙ ነው፡፡
-እንዳለጌታ ከበደ “ጽላሎት” በሚለው መጽሐፉ አሥራ አንድ ትርክቶችን ያስነብበናል፡፡ ነገር ግን “አርባ ደቂቃ” በሚለው ጽሑፉ አንድን ካህን መሐይም ፣ደደብ :ነገር የማይገባው ለጊዜ ያላቸው ቦታ በጣም ዝቅተኛ በማድረግ ያቀርባቸዋል፡፡ (ጽላሎት፣ገጽ 67-77) በጽሑፉ ካህኑ የኋላ ቀርነት ውክልና ነው ያላቸው፡፡ ካህኑን በኔ አረዳድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ንን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ቤ/ን የኋላ ቀሮች መጠራቀሚያ እንደሆነች ማሳየት ይመስላል፡፡ የድድብና ድንቁርና የኋላቀርነት ነገር የማይገባቸው ተምሳሌት ውክልና በገጸ ባሕርያት የሚሰጣቸው ብቹ ጊዜ ካህናትን ነው፡፡
- ለምን ካህናትን ? የሰለጠኑ ነገር የሚገባቸው ልሒቃን የሆኑ ካህናት የሉም? አዋቂዎቹን ለምን በጎ ነገራቸውን ማሳየት አይፈለግም? በመካከለኝነት መንገድ መግለጽ አይቻል ይሆን? እርግጥ ደራሲያን መብት አላቸው የፈለጉትን የመጻፍ፡፡ ነገር ግን ሥነ ጽሑፍ የትውልድን አስተሳሰብ ይቀርጻልና ለወደፊቱ ስጋቴ ለካህናት የማይምነትና ድንቁርና ውክልና የሚሰጥ ትውልድ አሁን አለ እንዲሁም ወደፊት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡
-በእንዳለጌታ ሥራ ብቻ አይደለም ሌሎች ብዙ ጸሐፍትም ካህናትን የሚወክሉት በአላዋቂነት ነው፡፡ ገጸ ባሕርያትንም ሲያናግሩ ካህናትን ምሥጢር እውቀት የማይዘልቃቸው የማይገባቸው ያደርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ በዓሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” በሚለው ልብወለድ ሥራው ላይ ሊቀ መንበሩን ሲያናግር “የደብተራ ጋጋታ ቅዳሴውን አያሳምረውም፡፡ ደባትር እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ማርክስና ሌኒንን የሚያነበንቡ ምስጢሩ ሳይገባቸው ተሳስተው የሚያሳስቱ እንደ ጥንቱ ደብተራ ጠዋት በቀኝ እጃቸው እያማተቡ ቀኝ ግራ እጃቸውን እንደ ሰይፍ የሚመዙብን ደባትር ብዙ ናቸው፡፡”(ገጽ 25) ይላል፡፡ “የህሊና ደወል” በሚለው ልብወለድ መጽሐፉም ደብተራን ምን ገጸ ባሕርይ እንደሰጣቸው ብናስተውል ተመሳሳይ ነው፡፡
-የፖለቲካ ጽሑፍ ቢሆንም አንዳርጋቸው ጽጌ “ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ” በሚለው መጽሐፉ “…በጨለማው ዘመን በነበረው የደብተራ የእውቀት ባህል ተተብትቦ፣ከአብርሆት ተጣልቶ በመኖር ብቻ የሚገለጽ አውዳሚነት አይደለም፡፡”(ገጽ 29) ይላል፡፡ የካህናት እውቀት የጨለማ ዘመን ነው በአንዳርጋቸው ሐሳብ፡፡ ካህናት ከድሮ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ማይም ምንም የማያውቁ ናቸው ማለቱ ነው፡፡
-የሥነ ጽሑፍ ሰዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች ለካህናት ወይም ደብተራ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ሚዛናዊነት ያጣ ነው፡፡ ለመሆኑ ደብተራው መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ዶክትሬት ዲግሪ አለኝ የሚልን የአባ አየለን ጥናት በአመዛዛኝና ሞጋች እእምሯቸው ገለባ እንዳደረጉለት አንዳርጋቸው ጽጌ ስለማወቁ እጠራጠራለሁ፡፡ አንድ አመዛዛኝ የሆነ ከደብተራ አድማሱ ጀንበሬ ጋር በአመዛዛኝነቱ ሊጠራው የሚችል ዲግሪ የተሸከመ የዘውግ ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ሊጠራ ይችላል? የደብተራ እውቀትን በጨለማ ዘመን የነበረ የሚለው፡፡ ብቻ ያደክማል ለካህናት ያላቸው አመለካከት ያሳፍራል፡፡
-ወፍጮ የሠሩትን የደቂቀ እስጢፋኖሱን አባል የነበሩት ወደ ቀደመው አስተምህሮ የተመለሱት ሊቁ አባ እዝራን ማን ይሆን ታሪካዊ ልብወለድ የሚያስነብበን? አባ እዝራንና ሌሎች የቤተመንግሥት አማካሪ የነበሩ ካህናትን ማን ይሆን በሥነ ጽሑፍ ሊያጎላቸው የሚችለው? ካህናትን ደንቆሮ አድርጎ ከመሣል ወጥተን አዋቂነታቸውንስ ማን ያሳየን? ወይም ማዕከላዊ የሆነውን መንገድንስ ማን ያሳየን ?
-ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ወዳጄ ልቤና ሌሎችም” በሚለው መጽሐፋቸው “አዲስ ዓለም” ሚል ልብወለድ አላቸው፡፡ በዚህ መጽሐፋቸው አወቀ የሚባል ሰው ካህናት ተዝካር ላይ የሚያደርጉት ነገር ተመልክቶ አስተያየት መስጠት ጀመረ ነገር ግን እነ መምሬ ሰባጋዲስ ሊቀበሉት አልፈለጉም፡፡ አወቀ ተዝካር ይቅር አያስፈልግም የሚል ሐሳቡ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ምእመናን በጣም ብዙ የሚበላና የሚጠጣ ያመጣሉና ይህ ተገቢ አይደለም ብዙ እየጠጣችሁ እየሰከራችሁ በሰዎች መዘባበቻ እየሆናችሁ ነው በመጠኑ እንዲመጣ አድርጉ፡፡ ክርስቲያኖች ብዙ የሚያመጡት ቀንሰው ገንዘብ ይስጧችሁ ለቤተሰባችሁ ይላቸዋል፡፡ በኋላ ይህ ሐሳብ ሌሎች ካህናትም ሰምተው ጉባኤ ተካሄደ ውሳኔም ሰጡበት ተራማጅነታቸውንም አሳዩ፡፡ መምሬ ሳባጋዲስም አስተሳሰባቸውን ቀየሩ፡፡ የአወቀ ሐሳብ ጠቃሚ እንደሆነ ተረዱ፡፡(ወዳጄ ልቤና ሌሎችም፣2002 ዓ.ም፣ገጽ 175-228)
-"አዲስ ዓለም" ልብወለዳቸው ላይ ብላቴን ጌታ ኅሩይ የመካከለኝነት መንገድን ተከትለው በልብወለድ መልኩ የካህናትን አስተሳሰብ ማሳየት ችለዋል፡፡ አላዋቂ ነበር ሲማርና ሲያውቅ ግን ማወቅ እንደቻለ ችግርን ራሳቸው ካህናት ጉባኤ ጠርተው እንዴት መፍታት እንደቻሉ ሁሉ ማሳየት ችለዋል፡፡ እኔ በካህናት ላይ ቢጻፉ ከምላቸው አካሄዶች የኅሩይ የመካከለኝነት መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ደንቆሮ፤ ነገር የማይገባው፤ ማይም ብቻ አድርጎ ማቅረብን ግን ትውልዱ ላይ በካህናት ላይ የሚፈጥረው አስተሳሰብ አደገኛ ነው፡፡ የሐዲስ ዓለማየሁ ድርሰት በሆነው በፍቅር እስከ መቃብር ያሉትን ቄስ ሞገሴን አሁን መሰዳደቢያ ሁነዋል ያሳዝናል፡፡ አቋም የሌለውን ሰዎች የሚሉትን ብቻ የሚሰሙ የራሳቸው ሐሳብ የላቸውም ብለው የሚያስቡትን መስሎ አዳሪን ሰው ቄስ ሞገሴ በማለት ለስድብ ሲጠቀሙ ማየት ያስተዛዝባል ያሳፍራል፡፡ ማንም ይሁን ማን በምሥጢረ ክህነት የከበረን ካህናት ስም ተጠቅሞ መሳደቢያና ማንጓጠጫ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ እናም ለምን ካህናትን? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
-ምንጭ: ዮሰፍ ፍስሃ ለ መጽሃፍ ትሩፋት

About the Author