#ጠበኛ_እውነቶች
የቅርብህ የኔ የምትለው የቱን ነው? በየዕለቱ የምታገኘው ወይስ በልብህ ማህደር በክብርና በፋቅር ለሁሌም የተፃፈ?በተለጣፊ ጆሮህ የሚሰማህ አልያስ በልብ ከልብ የሚሰማህ?
አንዳንድ ያንተ ሰው አለልህ
በአካል ለብዙ ግዜ ላታገኘው ትችላለህ። ስትገናኝ ለምን እንደተጠፋፋህ በመዘብዘብ ግዜ አታባክንም። ቅድም እንደተገናኘህ ሁላ ካቆምክበት ትቀጥላለህ። "ከዓይን የራቀ" ፈሊጥ ለእንዲ አይነቱ ያንተ ሰው አይሰራም። የጊዜና የቦታ ርቀት በወዳጅነትህ መሃል የልብና የደረት ያክል ክፍተት የለውም። ያን የምታውቀው በህይወትህ ሁለቱ ዋልታ ላይ ስትሆን ( ስትፈነጥዝም ስትከፋ ) አጠገብህ በየቀኑ ኖሮ ለልብህ ከራቀው ሰው ይልቅ። ስልክህን የምታጮኸው ለእሱ ሲሆን ነው። ከልብ የፈለቁ ቃላት የሚለበልብ ቁስልህን ያደርቅልሃል።አይቶህ ያውቅሃል። ቃል ሳታባክን ትገባዋለህ።
እውነታው ሰዎች ሊየወድሱህ ከፈለጉ ከፈጣሪ ታናሽ ያደርጉሃል። ሊዘልፉህ ከፈለጉ ደግሞ ሳጥናኤል የሚቀናበት ክፉ ያደርጉሃል። ከሰማሃቸው ደግሞ ራስህን የመሆን እድል አይሰጡህም። ሁሉም በፈለጉት መንገድ ሊቀርፁህ መጥረቢያ ይስላሉ። ልብህን ከከፈትክላቸው የየድርሻቸውን ጠርበውህ ቅርፅ አልባ ያደርጉሃል።
ሰዎች በየቦታው ፍፁም ትክክል መስለው ሲታዩ ሰውኛ አይመስሉኝም። ከራስ የተቧቀሱ አካባቢው በቀረፀለት የትክክለኛነት ሳጥን ውስጥ የሚንፈራገጥ ሰው ራሱን ያጣ አሳዛኝ ይመስለኛል። ለእያንዳንዱ ነገሩ የሚጠነቀቅ ሰው ራሱን እየሆነ እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ። ራስን መሆን እርማት አይጠይቅም።ራስን ለመሆን ጥንቃቄ አይሻም። መጠኑ ቢለያይም ሁላችንምጋ ጥቂት እብደት ፣ ጥቂትም ስህተት ፣ ጥቂትም ፀፀት እና ጥቂትም ውድቀት አለ ብዬ አስባለሁ።
የሰውን ልጅ ሁሉ መውደድ። እራሴን እወዳለሁ ለዛ ነው ሌሎችን የሚወድ ልብ ያለኝ። ለራሱ ፍቅር የሌለው ለሌላ ተርፎት የሚለግሰው መውደድ። አለው ብትሉኝ ያንቀኛል። በሰውኛ ልኬት ሰውን የመውደድ ጣሪያ ራስን ከመውደድ ልክ መሆኑን ለማሳየት ይመስለኛል ክርስቶስ ከህግ ሁሉ የበላይ ህግ የትኛው መሆኑን ሲጠየቅ 'ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ' ያለው። የፈጣሪ ትርጉም ለኔ ፍቅር ነው። የማላየውን ፈጣሪ ማምለክ እናት መውደድ በአምሳሉ በፈጠራቸው በሰዎች ሁሉ ውስጥ አለ ብሎ ማመን እነሱን ማክበርና መውደድ ነው። ፍቅር ከክፍት በብዙ የራቀ ነውና ።
በልባቸው ጠብታ ቅንነት ሳይኖር ለፍቅርና እግዜርን ለመፍራት የሚኖሩ ያስመስሉታል። ...ከክፉ ልብ ከመነጨ ምርቃት ይልቅ በአንድ ልኩ ከቅን ልብ የሆነ እርግማን ይሻላል።
የገባኝ ነገር በመርሳት ውስጥ ማስታወስ መኖሩ ነው። ለመርሳት መሞከር ራሱ በብርቱ ማስታወስ ነው። መርሳት የሚቻለው መርሳትን ራሱን በመርሳት ነው።
ሁሉም ሰው በልቡ ለማንም ማሳየት የማይፈልገው ቆሻሻ ይኖረዋል ጥላቻ ፣ ክፍት ፣ ግልፍተኝነት ፣ ራስን መውደድ ....አንዱ ይኖርበታል ። ልዩነቱ ብዙዎቻችን ያ ባህሪያችን በአስገዳጅ ሁኔታ ፈንቅሎን ካልተገለጠ በስተቀር ንፁህ ፣ ቅን እኔ ፍፁም እንደሆንን እናስመስላለን።
የሰው ልጅ ሁሉ ከትላንቱ ተጋብቶ ሳይሆን አይቀርም የሚኖረው። ዛሬው የትናንት ጭማቂ ነዋ!! የዛሬ ግቡ የትናንት ምክንያቱ ነበራ!
ሲገባኝ ሁሉም ሰው " የለውጥ ኩርባ" አለችው። አስተሳሰቡ ወይ ስሜቱ ወይ ድርጊቱ የሚቀየርባት።ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚታጠፍበት ወይም ከወደቀበት መቀመቅ የሚስፈነጠርበት ወይም ለዛለው ጉልበቱ አቅም የሚያገኝበት። ለውጥ ወደ ተሻለ ማደግ ብቻ አይደለምና ኩርባውን ሲታጠፍ ውድቀትም ሊሆን ይችላል። ያቺ የለውጥ ኩርባ አንድ የሆነች ኢምንት ክስተት ልትሆን ትችላለች ወይም ዓረፍተ ነገር ወይም ...
በቀኖችህ ውስጥ ለምታደርገው ትግል ጥያቄው መሽነፍህ አይደለም። መዋጋትህ እንጂ። ምክንያቱም ሳትታገል ሁሌም ውጤቱ የታወቀ ነው። ተሸናፊ ነህ። በትግልህ ውስጥ ውጤቱ ከሁለቱ አንዱ ነው ። ማሸነፍ ወይ መሸነፍ!! ጥያቄው መዋጋትህ ብቻም ላይሆን ይችላል።የተዋጋህለት አላማ እንጂ።
ብዙ ግዜ የሰቀልከው ተስፍጋ ለመድረስ መንጠራራት ተስፍውን ከመጨበጥ በላይ ደስታ አለው።ጉልበትና የተስፋ ስንቅ ያጅቡታል።
ሁሉም የህይወት ገፅ መጨረሻ ላይኖረው ይችላል። ለህይወት መጨረሻ ብሎ ነገር የለም። የአንድ ቀን መጨረሻ የሌላው ቀን መጀመሪያ ነውና። የሰኞ ማለቅ የማክሰኞ መጀመር እንደሆነው። የምድር መጠቅለል ለሰማያዊ ህይወት መጀመር እንደሚሆነው።
በእያንዳንዱ ክፋት ጀርባ መሪር በደል አለ....ጥያቄው የሚሆነው በደልን ይቅር ያለ በጎነት የለም ወይ? ...ኖሮ ያውቅ ይሆናል ። በደልን ይቅር ለማለት የሚያስችል ትልቅ በጎነት የሚፈጥር ፍቅር የሚጠይቅ ይመስለኛል።
ዓለም ራሷ ክብ አይደለችም? ኑረትም እንደዛው መሰላኝ። አንድ ዒላማ ላይ መሽከርከር ። ሽክርክሪቱ ያው ቢሆንም ሁሉም ሰው የሚሽከረከርበት መሃለኛ ነጥብ አለው።የታደሉት የሽክርክሪታቸው መሃለኛ ነጥብ ስህተት መሆኑ ሲገባቸው ወይም ሲሰለቻቸው። አልያም ተስፍ ሲቆርጡ ዒላማቸውን ይቀይሩትና አዲስ ሽክርክሪት ይጀምራሉ።
በተለያየ መኝታ በተለያየ እንቅልፍ ውስጥ አንድ አይነት ህልም እንዴት ይታለማል ? የሆነ ሰው ያለፈበት መንገድ እና የደረሰበት ስኬት እንዴት የሌሎች ብዙዎች መንገድና መድረሻ ይሆናል?የሌሎች ብዙዎች ደስታ በአንድ ሰው መዳረሻ እንዴት ይጠፈራል?
ሁሌም ዛሬ ላይ ቆመህ ሁለት ምርጫ አልህ ። ትናንት ወይ ነገ ፤ ትዝታ ወይም ተስፋ!
"#ምርጫ_አልባ_ምርጫ"
ብሩህ ነገ የሚባል ቀን የለም። ማንም ቢሆን ነገን ኖሮ የሚያውቅ የለም። ምክንያቱም ነገን ለመኖር ስንጀምር ዛሬ ተብሏል። ብዙዎቻችን ግን ሁሌም ብሩህ ነገን ለመኖር ስንናፍቅ ብዙ ዛሬዎችን ያልፈናል።እናም ብሩህ የሚባል ቀን ሳይኖረን እናልፋለን። ብሩህ ቀን በእጃችን ያለው ዛሬ ነው።
ማወቅ ከባድ አይደለም መኖር እንጂ! ያወቁትን ሁሉ መኖር የሚቻል ቢሆን ኖሮይህች አለም ከብዙ ስህተቶችና ጥፋቶች በተረፈች ነበር።
ምንጭ ፦ ጠበኛ እውነቶች
ደራሲ ፦ ሜሪ ፈለቀ