ባይተዋርነት (estrangement) የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አትኩሮቱን ካዳረገባቸው መሰረታዊ ርእሰ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህ ርእሰ ጉዳይ በአዳም “ግራጫ ቃጭሎች” የፈጠራ ሥራ፣ በዋናው ገፀ-ባሕሪ መዝገቡ ዱባለ ታሪክ ውስጥ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ታሪኩ ውስጥ ገፀ-ባሕሪው በንፋስ መውጫ ሳለ የልጅነት ጊዜውን ከሰው ርቆ ከሚኖርበት ከተማ መሐል ከሚገኘው ጉብታ ላይ ዘወትር ብቻውን ተቀምጦ በመዋል ጊዜውን ያሳልፍ ነበር፡፡ እንደ ኤግዚስቴንሻሊዝም አስተምህሮ አንዱ የባይተዋርነት (estrangement) ስሜት መነሻ፣ ግለሰቡ ከሚኖርበት ማህበረሰብ ጋር ያለው የሞራልና የአመለካከት ርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የመዝገቡ የብቸኝነት (ገለልተኝነት) ስሜት መነሻ አብሮት ከሚኖረው ማህበረሰብ ጋር ያለው የህልውና ርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ ነው፡፡
… ይህ ሁሉ ሕዝብ የዚችን ፀሐይ አወራረድ ሳያይ በየቤቱ ሲገባ ቅር አይለውም እላለሁ፡፡ በየቤታቸው ምን ይሠራሉ እላለሁ፡፡ የሚሠሩትን አስቤ አስቤ ከጥቂት ነገሮች የበለጠ መዘርዘር አልቻልኩም፡፡ ይኼ ሁሉ ሕዝብ እነዚህን ትንሽ ትንሽ የመሠሉ ነገሮች ይሠራል፡፡
ራት ይበላሉ (ካልበሉ ስለሚራቡ)
ይጠጣሉ (ካልጠጡ ስለሚደርቁ)
ይጫወታሉ (ካልተጫወቱ ስለሚያብዱ)
ይተኛሉ (ካልተኙ ስለሚደክማቸው)
ያወራሉ (? )
እኔ በማትደክም ቂጤ ተቀምጫለሁ፣ በማይደክሙ ዐይኖቼ ዙሪያ ገባየን አያለሁ፣ እዚያው እንደተቀመጥኩ ይመሻል፡፡ ጥቁሩን ሰማይ ማጥናቴን እቀጥላለሁ፡፡ ከዋክብት እቆጥራለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከዋክብት ለመቁጠር እሞክራለሁ (አዳም፣ ግራጫ ቃጭሎች፣ ገፅ4፣ 1997)።
ወዳጆች መፅሐፉን በማንበብ ሃሳቦቹን ትጠቀሙባቸው ዘንድ ግብዣዬ ነው!
መልካም ንባብ!
ቸር ጊዜ!
__________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ