
ዳሰሳ፡- የአዲስ አበባ ውሾች፤ ደራሲ፡- ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ፤ የገጽ ብዛት 253 (pocket size)
ዋጋ 100 (አንድ መቶ ብር 2ኛ ዕትም)
በእንቶኔ ዘይቤ፤ በሁሉን አወቅ አንፃር የትረካ ስልት የቀረበ ልብወለድ መጽሐፍ፡፡
የታሪኩ ማጠንጠኛ፡- ለመጽሐፉ ጭብጥ ጠቃሚ የሆነ የኋላ ታሪክ ያለቸው ጌቶቻቸው፤ ከሥራዎቻቸው የተነሳ ባጋጠማቸው ችግር ለጎዳና የተሰጡ ውሾች ሕይወት ነው፡፡
ጌታው ባለ ሥልጣን የነበረ ውሻ አለ፡፡ በስልጣኑ በመባለጉ ዘብጥያ ሲዎርድ፤ ቤተሰብ ሲበተን ውሻውም ዕጣ ፈንታው ጎዳና ሆነ፡፡ ጌታው ነጋዴ የነበረ፤ ከባለስጣናት ጋር በመተሳሰር ከግብር ነፃ፤ ከጨራታ ነፃ፤ ከቀረጥ ነፃ፤ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት ሲንደላቀቅ የኖረ ሀብታም ጌታው፤ የዓይነ ስውሯ ፍትህ ሰይፍ አርፎበት፤ ወህኒ ሲገባ በመኪና ሲንደላቀቅ፤ ሬስቶራንት ሲባለ … የነበረው ውሻው ጎዳና ላይ የተጣለ አለ፡፡ ዲያስፖራው ጌታው ብር ብቻ ይዞ መጥቶ፤ በብዙ ምከንያቶች በመክሰሩ ዓለምን ሲዞር የነበረ ውሻውን ትቶት በመሄዱ ጎዳና ላይ የወደቀ ዲያስፖራ ውሻ አለ፡፡ ደግሞ ከቤተ ክህነት የተገፋ ሊቅ ጌታ የነበረው ሊቅ ውሻ አለ፡፡…. እዛው ጎዳና ላይ የነበረ የአራት ኪሎ አራዳ ውሻ ደግሞ አለ፤ ሌሎችም፡፡
እነዚህ እነ ንካው፣ “አሜይዚነግ” ማለት የሚወደው ሉሉ፣ “አሎራ!” ከአፉ የማይጠፋው ጆዜ፣ ግዕዝ ተናጋሪውና ቅኔ ዘራፊው ዑቃቤ፣ “ሹክራን” የሚለው ባሲል እና ሌሎችም አስገራሚ ውሾች ናቸው፡፡ ታሪካቸውም ትረካቸውም ይጣፍጣል፡፡
ሌሎች ደግሞ ነፃ አውጪ ውሾች አሉላችሁ፡፡ የካዛንቺስ ነፃ አውጪዎች፤ የአራት ኪሎ.. ወዘተ፤ እነዚህ ተደራጅተው ውሾችን ያሳድዳሉ፡፡ እኛ ነፃ ባወጣነው ሠፈር ይላሉ፡፡ ስንት ውሾች ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱ ታያላችሁ፡፡ ተሰዳጆቹ ይጠይቃሉ “እኛም ውሾች፤ እናንተም ውሾች፤ ለምንድነው ውሻ በውሻ ላይ የሚጨክነው?”
ውሾቹ ዕጣ ፈንታቸው ከሰዎች ጋር ይመሳሰላል፤ የሰዎች ግፍ ዳፋም በቀጥታ አርፎባቸዋል፡፡ እንደ ቀበሮ ጫካ መኖርን ትተው፤ ሰውን እያገለገልን ከሰው ጋር እንኑር ባሉ ስንት መዓት እንደ ወረደባቸው እናያለን፡፡ የባለሀብቶቹ፤ የባለ ሥልጣኖቹ ውሾች፤ ስንት ጉድ ሲሰሙ ኖረዋል፤ ስንት ዱለታ ዓይተዋል፡፡ አይናገሩም፤ አይሰሙም እየተባለ፤ ጥግ እየተያዘ፤ ጓሮ እየተገባ፤ ጨለማ ተገን እየተደረገ፤ በስልክ የሚወራውን ሁሉ፤ ሲሰሙ እና ሲያዩ የኖሩትን እያነሱ ያዋራሉ፤ ያወጋሉ፡፡ ጨዋታቸውን በቅኔ፤ በምሳሌያዊ አባባሎች፤ በተረትተረት፤ በታሪካዊ ገጠመኞች፤ ከፊልም፤ ከመጻሕፍት፤ ከሙዚቃው ሁሉ እየጨለፉ በማዋዛት፤ ብርዱንና ረሃቡን እንዲሁም ስደቱን ያስታግሱታል፡፡
Product Details
Synopses & Reviews
ሁሉንም ያገናኛቸው ማጣት ነው፡፡ የመሰባሰባቸው ምከንያት መገፋት ነው፡፡ እነርሱ ራሳቸው በአስተሳሰብ አንድ ለመሆናቸው እርግጠኞች አይደሉም፡፡ ይት ነው የምንሄደው? ለሁሉም ግልጥ አይደለም፡፡ ምናልባት ይህ ነገር የተነሣ ዕለት ያለያየን ይሆናል ብለው ፈሩታል፡፡ ከየአቅጣጫው መምጣት ይቻላል፡፡ ወደየአቅጣጫው መሄድ ግን አይቻልም፡፡ ማንም ሲፀነስ ከአባቱ አብራክና ከእናቱ ማኅፀን ከተለያየ አቅጣጫ ነው፡፡ እነዚህ ከየአቅጣጫው የመጡ ነገሮች ግን በኋላ ወደ አንድ አቅጣጫ አንድ ሰው ሆነው ነው የሚጓዙት፡፡ ለመምጣት አንድነት አያስፈልግም ለመሄድ ግን የግድ ነው፡፡” ገጽ 113
የውሾቹ ትዝብት
“ሀብት፣ ዘርና ሥልጣን ኃጢአትህን ይሸፍንልሃል፡፡ ድህነት ደግሞ ኃጢአትህን ያጋልጥብሃል ማለት ነው፡፡ ሼም ጠፍቷል ጀለሴ፡፡” በብዙ ኃጢአት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ጭምር የሚከበሩ ባለሀብቶችን፤ ያነሳሉ፤ እነሱ ለመጸለይ በተከለከሉበት ቦታ ሀብታሞቹ ይሰገድላቸዋል፡፡ እናም ሉሉ ይጠይቃል ““ክርስቶስ ያባረራቸውን ሻጮችና ለዋጮች፤ ሕንጻ እየሠራ፤ በቤተ ክርስቲያን ዙርያ መልሶ ማን እንደሰበሰባቸው ሳስብ አሜዚን ይሆንብኛል፡፡ ቤተ ክረስቲያን ለድሆች ማደርያና መመገቢያ፣ ለአረጋውያን መጦሪያ፣ ለድሃ ተማሪዎች መማሪያ፣ ለዓቅመ ደካማ ሕሙማን መታከሚያ፣ መቼ ነው የምትሠራው?” አለ ሉሉ፡፡ ጆዜ ዝም ብሎ ይሰማቸዋል፡፡” ገጽ 44-45
ይሄው ሉሉ የተባለ ውሻ ከዘበኛቸው የሰማቸውን በርካታ ታሪኮች እና አባባሎች ያጋራል፡፡
“ሀገሬ ዳገትሽን በዳዴ ልለፈው
ሁሉም የግል ሆኗል ምኑን ልደገፈው ይሉ ነበር” ይለናል፡፡ ገጽ 93
“በናቷ ሽምብራ በአባቷ ባቄላ
የሁለት ጥሬ ልጅ ኧረ እንዴት ትበላ አለ ዘፋኝ” ገጽ60
“እከክ ብቻ ሆኗል እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መቀመጫ መሄጃ ያጣል ሰው” ገጽ 125
በመጨረሻም ወደረኞቻቸውን በሐሳብ ይሞግታሉ፡፡
ይላሉም “ነጻ አውጭነት ታጋይነት ከሆነ የምትታገለው ወገንህ የተሸለ ነገር እንዲያገኝ ነው፡፡ …… ነጻ አውጭነት ንግድ ሲሆን ግን ጉዳዩ የትርፍና ኪሣራ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ሌላ ሰው እንዲያተርፍ ብሎ እርሱ የሚነግድ የለማ፡፡ ነጋዴ ነጻ አውጭም የሚታገለው ራሱን በቀደምቶቹ በዝባዦች ለመተካት ነው፡፡ ለዚህ ነው ውሾች የሚነክሱን ውሾች ያየነው፡፡ ጅቦችስ ከዚህ ውጪ ምን ያደርጉብን ነበር?” ገጽ 124
ሙግት ብቻ አይደለም ውሾቹ መፈክርም አላቸው፡፡
““ለመመራት ዝግጁዎች ነን፤
ለመገዛት ግን ፈጽሞ!
ለአባሪነት ዝግጁ ነን፤
ለተገዥነት ግን ፈጽሞ” ሲል ባሲል ፎከረ፡፡ ሁሉም አካባቢው እስኪደባለቅ ድረስ ጮኹ፡፡ ….. ከወንዙ ማዶ አራት ሶለጎች ቆመው ያዩዋቸዋል፡፡ አስተያየታቸው የጤና አይመስልም፡፡
ሁሉም ሰው ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡ በተለይ በወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ላይ ተቀራራቢና ውጤታማ አስተሳሰብ ለማራመድ እጅጉን ጠቃሚ በመሆኑ ያላነበባችሁ እንድታነቡ፤ ያነበባችሁና የምታነቡትም ሁላችሁ ደግሞ ላላነበቡት በማድረስ ኢትዮጵያን እንድትራዱ እጠይቃለሁ፡፡
ክብረት ይስጥለን፡፡ ና ኦፍ ካልቻ! ዮሴፍ ከተማ