ሀበሻ ፍትሐዊ እንጂ ምቀኛ አይደለም
... በመካከል ጨዋታ ለመቀየር በማሰብ "ሺፌ ለምን ጉዳይ ነው ጭልጋ የምትሄደው አልኩት?"ሺፈራውን።
"ምን ባክህ አንድ ጤና ጣቢያ ለመገንባት ጨረታ አሸንፌ ሥራውን አጠናቅቄ ቀሪ ገንዘብ ለማስለቀቅ ርክክብ ሲደረግ አንድ ገገማ የሆነ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ነኝ ባይ አስቸግሮኝ ለእርሱ እየሄድኩ ነው።ከእናንተ ጋር ለመጫወት ብዬ ነው እንጂ የሳይት መሐንዲሴ ትናንት መኪናዬን ይዞት ሂዶ እየጠበቀኝ ነው"አለ።
"ምንድነው ነው ችግሩ?በዲዛይኑ መሠረት አልሠራችሁትም እንዴ?" አልኩት ።
ሺፈራው የማያሳምን ነገር ለረጅም ስዓት ሲነግረን ቆየና "ባክህ ተወው ዱሮም ሀበሻ ምቀኛ ነው: አሁን ትንሽ ሳልሰው አፉን ይዘጋል " አለ።
ዶ/ር ክብረ በዓል የሺፈራው ንግግር ስላልተመቸው ማዶ ማዶ ሲያይ ነበር።በመካከል <ሀበሻ ምቀኛ ነው > ሲል ግን ፊቱ ልውጥውጥ አለና:-
"ስማ ሺፈራው! በጣም ታሳዝናለህ! ያልዘራኸውን ስታጭድ: ያልከመርከውን ስትወቃ: ያላቦካኸውን ስትጋግር <ለምን?> ሲልህ <ሀበሻ ምቀኛ ነው> ትለዋለህ እንጂ ሀበሻ እኮ ፍትሐዊ ነው"።
"የህፃኑን ጡጦ : የአረጋዊውን ከዘራ : የእሙሀይቷን ምርኩዝ ስትቀማ : የድሀውን ጉሮሮ ስትዘጋ <ለምን?> ሲልህ ምቀኛ ትለዋለህ!
ስማ! ሀበሻ ፍትሐዊ እንጂ ምቀኛ አይደለም።"
"ከጭንቅላትህ በእጅጉ የገዘፈ ባርኔጣ ደፍተህ : ከእግርህ የረዘመ ጫማ አድርገህ : ከትከሻህ የሰፋ ካባ ደርበህ ልትኮፈስ ስትሞክር እርግጥ አያዳንቅህም ይልቁንም ሊሸረድድህ ይችላል። ያን ጊዜ <ተወው ባክህ ሀበሻ ድሮም ምቀኛ ነው> ትለዋለህ ።"
"አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቡን እንኳን በአግባቡ የማያስተዳድር ሰው የሀገር ሚኒስትር ሲሆን : ስሙን በአግባቡ መግለፅ የማይችል ሉዓላዊትና ጥንታዊት ሀገር እንዲወክል አምባሳደር ሆኖ ሲሾም : ምን ገዝቶ እንዴት ሸጦ ስንት አትርፎ እንዳደገ ሳይታወቅ በአቋራጭ የሀብት ማማ ላይ ሲቀመጥ : <እንዴ እንዴት ነው ነገሩ?> ሲል <ተወው እባክህ ዱሮም ታዳጊ ሀገር መፈጠር መከራ ነው> ትላለህ።"
"ጅማትህ እስኪኮማተር : ሳንባህ እስኪወጠር : ተረከዝህ እስኪነቃ : ወዝህ እስኪንቆሮቆር እንደ ሀይሌ ተፈትለክ : እንደ ደራርቱ ሩጥና ክበር ማን ይመቀኝሃል? ደራርቱ ወርቅ ብትለብስ ጥሩነሽና መሠረት ሀር ቢያገለድሙ ማን ይቃወማቸዋል ። ቀነኒሳ የወርቅ ዝናር ታጥቆ ቢዞር ኃይሌ በሕንፃ ላይ ህንፃ በፎቅ ላይ ፎቅ ቢያቆም ማን ቅር ይለዋል? ማንስ ዐይኑ ደም ይለብሳል ? አንተ ግን የሕዝብን ሀብት ዘርፈህ : የመንግሥትን በጀት ሞጭልፈህ : አየር በአየር ተንሳፈህ : በሀብት ለመንሳፈፍ ስትሞክር <ለምን?> ብሎ ሲጠይቅህ <ምቀኛ> ትለዋለህ ። "
"እውነታው ግን ከግብፅ ብትመጣም በመልካም ሥራህ <አቦ አቡዬ> ይልሀል።ግፈኞች ታሪክህን ቢሰቅሉት :-
"ተሰቀለ ቢሉኝ ዝናሩን ነው ብዬ
ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሰውዬ"
እያለ ስምህን ከመቃብር በላይ ያውላል።"
"ሀበሻ ውለታ የማይረሳ የዘመን ነፋስ የማይወስደው ሚዛናዊና ፍትሃዊ ህዝብ መሆኑን አትርሳ ። ሞለጭላጫ ዘመነኛ ጥባቴ የራሱን የረከሰ ምግባር ለመሸፈን የወጣበትን ባሕር ቢመርዘውም የውሃው ጣዕም የማይቀየር ጣፋጭ ነው "
ዝጎራ - ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ
Product Details
Synopses & Reviews
እባክህ ቁስላችንን የሚቀርፍ ሳይሆን የሚያክም፣ ትናንት ጦማችንን አደርን ስንለው ዛሬም ድገሙ የማይለንን ተቆነጠጥን ስንለው የማይኮረኩመንን ከፋንጰስንለው የማያስለቅሰንን የምንፈራው እርሱም የሚፈራን ሳይሆን ሁላችን ንደ አባት የምናየው አንድ ሙሴ ስጠን። ሕዝቡን አስከትሎ በኢትዮጵያ ተራሮች፣ ሸለቆዎች፣ ሜዳዎች፣ ሸንተረሮች የተቆለፈበትን ቁልፍ የሚፈልግ የአድባራቱንና የገዳማቱን ቡራኬ የሚቀበል፣ የአዛውንቶቹን፣ የሼኾቹን ምርቃት የሚያከብር፣ የምዕራብን ካፒታሊስት የምስራቅን ሶሻሊስት ርዕዮት ንደወረደ ተግቶ ኑ ልጋታችሁ የማይል የዚህችን ድንቅ ሀገር ምስጢር የሚፈታ አንድ ሙሴ ስጠን። (ዝጎራ)
About the Author
ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እሸቴ ይባላል በሙያው የስነ-ምህዳር እና የስነ-ህይወት ባለሙያ [ 𝚎𝚌𝚘𝚕𝚘𝚐𝚒𝚜𝚝 ] ነው።
በምርምር ስራው አንቱ የተባለ በአለም አቀፍ የስነ ህይወት ምርምር ላይ ባስመዘገበው አዲስ ግኝትም ( ATBC ) - 𝑎𝑠𝑠𝑜𝑐𝑖𝑎𝑡𝑖𝑜𝑛 𝑓𝑜𝑟 𝑡𝑟𝑜𝑝𝑖𝑐𝑎𝑙 𝑏𝑖𝑜𝑙𝑜𝑔𝑖𝑐𝑎𝑙 𝑐𝑜𝑛𝑠𝑒𝑟𝑣𝑎𝑡𝑖𝑜𝑛 በየ አመቱ የሚያዘጋጀውን
( የ2007 እ.ኤ.አ ) የአልወን ጆንትሪ ሽልማትን ያገኘ 𝑎𝑙𝑤𝑎𝑦𝑛 𝑔𝑒𝑛𝑡𝑟𝑦 𝑎𝑤𝑎𝑟𝑑 እና በየ ጊዜው የምርምር ስራዎቹን ከፍተኛ እውቅና ባላቸው ጆርናሎች የሚያሳትም ስመ ገናና ተመራማሪ ነው ።
መልካም ስብዕና ያለው ደግ ፣ ቅን ፣ ሩህሩህ ነው። ታይታ ፣ ውዳሴ ከንቱ ፣ ግብዝነትን የማይፈልግ መንፈሳዊ ሰው ነው ።
ሲያወራ ቀልብንና ልቦናን ይገዛል ፤ የማይኖረውን ህይወት የማይናገር ፣ የተናገረውን የማያስቀር የቃል ሰው ነው።
በጣም የሚገርመኝ የሰውየው ትህትና እንኳንስ ህያዊት ነብስ ያለውን የሰውን ልጅ ቀርቶ ደመነፍሳዊያን እንስሳትን እንኳን ይገዛል ።
ይህ ሰው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተራቆተውን መሬት በማጥናት ፣ መፍትሄ በማመላከት እንዲሁም የቤተክርስቲያንን እፅዋት በመለየት ፣ በማጥናት ለአለም አሳውቋል ።
- ከዘመኔ የስነጽሁፍ ገጸበረከቶች ውስጥ የሱን ስራ ስነፅሁፍ ( ድርሰቶች ) በመጀመሪያ ረድፍ የማስቀምጣቸው ስራዎች ናቸው።
- እነዚህን ፬ መጽሀፍቶች እናንተ ባታነቧቸው እንኳን ልጆቻችሁ ሊያነቧቸው ስለሚችሉ ገዝታቹህ እቤት አስቀምጧቸው ።መጽሀፍቶቹ በዘመናችን የሰው ልጅ የደረሰበትን የባህል ግጭት የእምነትና የሳይንስ ፍጭት አጉልተው የሚያሳዩና ለእኛ ዘመን ትውልድ የተበረከቱ የአዕምሮ ማረጋጊያ
[ 𝑚𝑒𝑛𝑡𝑎𝑙 𝑡ℎ𝑒𝑟𝑎𝑝𝑦 ] ናቸው ።
ጊዜህን ሰውተህ እንደ አውሬ ዱር ለዱር በመጓዝና ተራራ በመውጣት ዘመን የማይሽራቸው መጽሀፍቶችን ጽፈህ ስላስነበብከን እናመሰግናለን
ምንጭ ደሳለኝ ሽፈራው መኮንን ከ መጽሃፍት ትሩፋት