የገጣሚ፣ ደራሲና ሐያሲ ደረጀ በላይነህ ስም ሲነሳ ወደ ብዙዎቻችን አዕምሮ ፈጥኖ የሚመጣው "እኔና አዳም" በሚለው ርዕስ የሚታወቀው ምርጥ ግጥሙ ነው፦
አዳም መከረኛው እልፍ ዛፍ ታድሎ
አንድ ተከልክሎ፣
አንድ ቢያጣ ሳተ፣
አንድ ቢያጣ ሞተ፤
ለእኔ ለዕድለኛው
አንድ ተፈቅዶልኝ፣ እልፍ ተከልክሎ፣
እንዴት ብዬ ልሳት
ዙሪያዬ በሙሉ በለስ ተንጠልጥሎ?
ከላይ እንደጠቀስኩት ደረጀ ገጣሚ፣ ደራሲና ሐያሲ ነው። እስከአሁንም ዘጠኝ መፅሐፍትን አዘጋጅቶ ለንባብ አብቅቷል። አሁን ደግሞ አደፍርስን ጨምሮ ፣ዘመናዊ ልቦለዶች፣ ግለታሪኮችና የሕይወት ታሪክ መጻሕፍት፣ የገብረክርስቶስ ደስታንና የሌሎች ወጣት ገጣሚያንን ስራዎችን በተመለከተ "ኂሳዊ ዳሰሳ"በሚል ርዕስ አሳትሞ ለአንባቢያን በመፅሐፍ መልክ አቅርቧል።
ብዙዎቻችን የሀገራችን ኪነጥበብ ልክ እንደ ኢኮኖሚውም አድገዋል የሚባሉ ሀገሮች ከደረሱበት ኪነጥበባዊ ማማ ላይ ወጥቶ እንዲመነድግ እንመኛለን። ምኞታችን እውን እንዲሆን ግን ከእነርሱ ልምድ ትምህርት ለመቅሰም ፈቃደኛ አንመስልም፣ ወይም እነርሱ ዛሬ ወደደረሱበት ከፍታ ያለምንም ጥረት በአቋራጭ ለመድረስ እንሞክራለን።
ለኪነ ጥበብ ዕድገት የዘርፉን መስፈርት ያሟላ ኂስ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ሆኖም በሀገራችን ለኂስ ዲስፒሊን የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው ማለት እንችላለን። እንዲያውም ኅያሲ ማለት ነቃፊ፣ ተቺ፣ ስህተት ፈላጊ ፣ ባስ ሲልም ምቀኛና በሌሎች ስኬት ዓይኑ የሚቀላ ተደርጎ እስከመቆጠር ሁሉ ይደርሳል። ይህ ሁሉ የተሳሳተ ግንዛቤ ግን ደረጃቸውን የጠበቁ ኂሳዊ ሥራዎችን ጠቀሜታ ለአፍታም ቢሆን ሊያደበዝዙብን ዘንድ አይገባም። ወዳጃችን ደረጀ በላይነህም በዚህ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስብስብ ኂሳዊ ሥራዎቹን የያዘ መፅሐፉን አሳትሞ ለንባብ አብቅቶልናል።
ምንጭ ጌታሁን ሄራሞ መጽሃፍ ጥቆማ