መጽሐፈ ሚርዳድ

መጽሐፈ ሚርዳድ

Regular price
$4.00
Sale price
$4.00
Regular price
Sold out
Unit price
per 
Shipping calculated at checkout.

ፍቅር መልካም ምግባር አይደለም፡፡ ፍቅር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ከዳቦና ከውኃ፣ ከዓየርና ከብርሃን የበለጠ ፍቅር ያሻችኋል፡፡ ማንም በማፍቀሩ አይኩራራ፣ ይልቁንም ነጻ ሆናችሁ እንዲሁ በዘፈቀደ አየሩን ወደ ውስጥ እንደምትስቡትና እንደምታስወጡት ሁሉ ፍቅርንም እንዲሁ በነጻነት ልብም ሳትሉ ተንፍሱት፡፡ ፍቅር፣ ማንም እንዲያወድሰው አይሻም፡፡ ይልቁንም ለፍቅር የተገባ ልብ ሲያገኝ ያን ልብ ያወድስ ይቀድሰዋል እንጂ፡፡ ከፍቅርህ ወሮታ አትጠብቅ፡፡ ፍቅር በራሱ ለፍቅር በቂ ሽልማቱ ነው፤ ልክ ጥላቻ ለጥላቻ በቂ ቅጣቱ እንደሆነው ሁሉ፡፡ ከፍቅር ጋር ሒሳብ አትተሳሰቡ፡፡ ፍቅር ሒሳብ የሚያወራርደው ከራሱ ጋር ብቻ ነውና፣ ተጠያቂነቱም ለማንም ሳይሆን ለራሱ ብቻ !

ፍቅር አያበድርም፣ አያውስምም፡፡ ፍቅር አይገዛም፣ አይሸጥምም፡፡ ሲሰጥ ግን ሁለመናውን ይሰጣል፡፡ ሲወስድም ሁለመናውን ይወስዳል፡፡ መቀበሉ በራሱ መስጠት ነው፡፡ መስጠቱም በራሱ መቀበል ! እናም፣ ለዛሬም፣ ለነገም ለከነገወዲያም እንዲሁ ነው፡፡

ራሱን ሳይሰስት ለባሕሩ የሚለግስ የትኛውም ወንዝ፣ ዘወትር በባህሩ ደግሞ እንደሚሞላ ሁሉ እናንተም እንዲሁ ፍቅር መልሶ ይሞላችሁ ዘንድ ራሳችሁን አንጠፍጥፋችሁ ለፍቅር ስጡ፡፡

አዎን … የባሕሩን ሥጦታ ከባሕሩ የሚነፍግ ኩሬ መጨረሻው መበስበስም አይደል !? በፍቅር … ትንሽ ወይም ትልቅ የሚሉት ነገር የለም፡፡ ፍቅርን መለካት፣ መመተር … ለፍቅር ደረጃ ማውጣት ስትሞክር፣ ፍቅር መራር ትዝታዎቹን አስታቅፎህ እብስ ይላል...

በፍቅር ዘንድ … ትናንት ወይም ዛሬ፣ ዛሬ ወይም ነገ… እዚህ ወይም እዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ወቅቶች የፍቅር ወቅቶች ናቸው፡፡ የትኛውም ቦታ ቢሆን ለፍቅር ማረፊያነት የተገባ ! ፍቅርን … ወሰንም ሆነ ዳር ድንበር፣ ካቴናም ሆነ የተዘጋ በር አይገድበውም፡፡ የትኛውም መሰናክል ጉዞውን ያሰናከለው ፍቅርም በተቀደሰው የፍቅር ሥም ለመጠራት ባልተገባው፡፡

ዘወትር፣ ፍቅር ዕውር ነው ብላችሁ ስታወሩ እሰማለሁ፡፡ አዎን፣ አፍቃሪ በተፈቃሪው ላይ አንዳችም እንከን አያይም ማለታችሁ ነው፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ … ይሄ ዓይነት አለማየት የማየት ከፍታ ጫፍ ነው፡፡

በምንም ነገር ላይ እንከን አታዩ ዘንድ ምነው ሁሌ በታወራችሁ፡፡

አይይ … የፍቅር ዓይኖችማ … ንጹህ፣ የጠሩና ሰርስረው የሚያዩ ብሌኖች ናቸው፡፡ ስለዚህም ምንም እንከን አያዩም፡፡

አዎን … ፍቅር ዓይናችሁን ሲያበራው … ያኔ … ለፍቅራችሁ ያልተገባ ምንም ነገር አታዩም፡፡ በእርግጥም፣ ፍቅር አልባ የተንሸዋረረ ዓይን ብቻ ነው በሌሎች ላይ ስህተት ፍለጋ የሚተጋ፡፡ የትኛውም የሚያያቸው እንከኖችም … የሌላም ሳይሆን የራሱ ናቸው፡፡

ፍቅር አንድ ያደርጋል፡፡ ጥላቻ ይበትናል፡፡ ይህ የመሠዊያው ጫፍ የምትሉት ግዙፍ የአለት ክምር እንኳ፣ በፍቅር እጅ ባይያያዝ ተበታትኖ በበረረ ! ይሄ በስባሽ ገላችሁ፣ መፍረስን የመከተው፣ እያንዳንዷን የአካል ሕዋስ በጥልቅ ፍቅር ብትወዱ ነው !!! ፍቅር፣ በሕይወት ማራኪ ዜማ የሚደንስ ሰላም ነው፡፡ ጥላቻ … ጨካኝ የሞት ጥላ ያጠላበት የተቅበዘበዘ ጦርነት ነው፡፡ የቱን ትመርጣላችሁ - ፍቅርና ዘላለማዊ ሰላምን ወይንስ ጥላቻን እና ማለቂያ የለሽ ጦርነትን ? መላዋ ምድር እናንተ ውስጥ ሕያው ነች፡፡ ሰማየ ሰማያቱ እና የሰማየ ሰማያቱ አለቆች እናንተ ውስጥ ሕያው ናቸው፡፡ ስለዚህም ራሳችሁን የምትወዱ ከሆነ፣ ምድርን እና መላ ፍጡራኖቿን ውደዱ፡፡ እናም ራሳችሁን የምትወዱ ከሆነ ሰማያቱን እና አገልጋዮቹን በመላ ውደዱ፡፡

ከ“መጽሐፈ ሚርዳድ”