“ከንጋት ጀርባ” ስለ ብሩህ፣ አወንታዊ፣ እና ቆራጧ፣ ሣራ በላይ የስደት ሕይወት ይተርካል:: ሣራ የኪነ-ጥበባት ትምህርትን ለመከታተል ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሕልም ያላት የአሥራ ስድስት ዓመት ኢትዮጵያዊት ልጃገረድ ናት:: ግን አንድ ችግር አለባት- ቤተሰቦቿ አይፈቅዱላትም:: አንድ ቀን የአባቷ ሹፌር ወደ ትምህርት ቤት ሲወስዳት፣ ስለ ሕገ-ወጥ ደላሎች ሲያወራ ከጀሮዋ ጥልቅ አለ:: ከሳምንታት በኋላ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በመስኮቱ ዘላ ታመልጣለች:: ሕይወቷን በአስደናቂ ሁኔታ የሚቀይር ጉዞ::
ሣራ ከሹፌሩ ባገኘችዉ ትንሽ መረጃ፣ ወደ ሱዳን አደገኛ የመንገድ ጎዳናዎች ጉዞዋን ጀመረች:: በጉዞዋ ላይ ጥሩ፣ መጥፎ፣ አስመሳይ፣ ጨካኝ ሰዎች ወደ ሣራ ሕይወት ይገባሉ- ይወጣሉ:: ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች በየአንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ይገጥማታል:: አንዳድ ጊዜ ደግሞ በሌሎች ቡድን ውስጥ በማይታመን ሁኔታ ጥሩ ትስስር ይፈጥርላታል፡፡ ይህም ለሣራ ጥቂት ሥዕለ ኅሊና እና ግንዛቤ ይፈጥርባታል:: ደኅንነት- በቤተሰብ- በተኮለኛ ሁኔታዎች መካከል::
ወደ ሱዳን እንደደረሰች፣ ሣራ ሥራ አገኘች፡፡ በጣም አደገኛ ነዉ ብላ ላሰበችዉ ጉዞ ገንዘብ አጠራቀመች:: ወደ አስከፊዉ ቀጣይ ጉዞ- በሰኻራ- በረኻ በኩል ወደ ትዕግስት አስጨራሹ እና ረዥሙ ጎዳና፣ ወደ ሊቢያ መንገዷን ጀመረች:: መንገዱ ቅዠት እየሆነ መጣ፡፡ ሣራ እና አዲሶቹ ጓደኞቿ ከአንደኛው አደጋ ሲያመልጡ ሌላኛዉ ላይ ይወድቃሉ:: አል-ኩፍራ ላይ ሕገ-ወጥ ደላላዎች ከአንድ ባዶ ቤት ዉስጥ ጥለዋቸዉ ጠፉ:: ጓደኟማቾች ወደ ትሪፖሊ እንዲወስዳቸዉ ኮንትሮባንድ የሚሠራ የአካባቢዉን ሰዉ ይቀጥራሉ:: እሱ ግን ወደ መሃል በረኻዉ ወሰዳቸዉ፤ ምድረ በዳ ላይ፣ ከሚገምቱት እና ካሰቡት በላይ ወደ አደጋ …
ሣራ ሕልሟን ታሳካለች? ሁኔታዎች፣ ፈተናዎች፣ የሷን ህልም እንዲያሰናክሉት ትፈቅዳለች? ምን ያክል ትጓዛለች? በዚህ ልብ አንጠልጣይ ታሪክ ዉስጥ ይፈልጉ:: እዉነተኛ ታሪክ::
Product Details
Synopses & Reviews
ከንጋት ጀርባ ÷ ባንድ በኩል÷ሕገወጥ የስደት ሕይወት እና የሻገተ የብሔር ፖለቲካ በተቃርኖ ተጣምረው÷ የትውልዱን ሥጋና መንፈስ እንዴት እያረከሱት እና እያመከኑት እንዳሉ የተገለጠበት፤ በሌላ በኩል÷ የሃይማኖት ልዩነትን ያሸነፈ ሰዋዊ ፍቅር እንደወረደ የተቀነቀነበት መጽሐፍ ነው፡፡ እናም÷ የሀገር ልጅነት፣ ሰዋዊነት እና ብሔርተኝነት÷ የመለያያም ሆነ የመገናኛ ድንበራቸው የት ድረስ እንደሆነ ከልቡናቸዉ የሚጠይቁና የሚያጠይቁ÷ አስተዋይ ወጣቶች እንዲፈጠሩ መጽሐፉ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው (ፒኤችዲ)
የፎክሎር እና የሥነ ጽሑፍ ተማሪ ወአስተማሪ